ኢተምድ የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀሙን ገመገመ

ኢተምድ የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀሙን ገመገመ

ኢተምድ በ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 4‚324 አገልግሎቶች በላብራቶር፣ በውጪና አገር ውስጥ ምርት ኢንስፔክሽንና በሠርተፊኬሽን አገልግሎቶች እንዲሁም በጁቡቲ ወደብ በኩል የኢንስፔክሽን ስራ 294,300 ሜትሪክ ቶን የስንዴ እና የአፈር ማዳበሪያ ኢንስፔክሽን አገልግሎቶች በመስጠት ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት እንዲኖር እና በጥራት ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ የግብይት ስርዓት እንዲኖር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

የኢተምድ የስራ እንቅስቃሴ አሁን በደረሰበት ደረጃ ሲታይ፤ ዓለም አቀፍ እውቅና የማስፋትና እውቅና የማግኘት ስራዎች በተመለከተ፣ ኮቪድ-19 በሃገራችን መከሰቱን ተከትሎ ጉዳት ካደረሰባቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ የአምራች ዘርፍ በመሆኑ እና ኢተምድ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ከአምራች ዘርፉ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው መሆኑ ስራዎች በተያዘላቸው እቅድ መሰረት እንዳይከናወኑ ቢያደርግም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እንደ ዝግጅት ምእራፍ ጥሩ የሚባል አፈፃፀምን አስመዝግቧል፡፡

 ድርጅቱ የሩብ ዓመቱን አፈፃፀም በገመገመበት ወቅት ተቋማዊ አደረጃጀትን በሠው ኃይል እና በግብዓት የማደራጀት፤የተቋሙን አገልግሎቶች ማስተዋወቅ፣ በሁሉም ዘርፍ ያሉትን የዓለም አቀፍ ዕውቅና የማግኘት እና ማስቀጠል ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ፣ከባለድርሻ አካላት ጋር በቁርጠኝነት እና በትጋት ተቀናጅቶ ለአገራዊ ውጤት በጋራ መስራት እና ለዓለማችን የጋራ ችግር የሆነውን ኮቪድ-19 ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ለመዋጋት በሚደረገው የአገራዊ ምላሽ ማዕቀፍ ውስጥ ተቋማዊ ሚናን ለይቶ እያደረገ ያለውን በማድነቅ ቀጣይነት እንዲኖረውም ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በምርትና አገልግሎት ጥራት ላይ የዛሬው የሰለጠነ ዓለም ላለበት ሁኔታ የሚመጥን ስራ እንዲሰራ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተገቢውንና የተሻለ የጥራት አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ፤ የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት አድርጎ የማይሰራ ተቋም  ወይም በምርቱና በአገልግሎቱ ያልረኩ ደንበኞች ወይም ባለድርሻ አካላትን ይዞ የሚጓዝ ማንኛውም በመንግስትም ሆነ በግል ዘርፍ የሚገኝ ድርጅት አደጋ ውስጥ መሆኑን በመገንዘብ የደንበኞች ፍላጎትን ለማርካት ተገቢውን ትኩረት ተሰጥቶት መስራት እንዳለበት ተገምግሟል፡፡