ኢተምድ የ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀሙን ገመገመ!

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ብቃት ያለው የላብራቶር ፍተሻ፣የኢንስፔክሽንና የሰርቲፊኬሽን አገልግሎቶችን በማደራጀት አምራች ድርጅቶች፣አገልግሎት ሰጪዎች፣ከሀገሪቱ ወጪ እና ገቢ ምርቶች አግባብነት ያላቸውን ብሄራዊ ወይም ዓለም አቀፍ ወይም የሌሎች ሀገሮች ደረጃዎችንና ህጋዊ መስፈርቶችን ማሟላታቸውን በመመርመር የተስማሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት በመስጠት ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት እንዲኖር እና በጥራት ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ የግብይት ስርዓት እንዲኖር በማስቻል የአገራችንን የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

   ኢተምድ በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 3‚983 አገልግሎቶች በላብራቶር፣በወጪና ገቢ ምርቶች ኢንስፔክሽንና በሠርተፊኬሽን አገልግሎቶች እንዲሁም በጁቡቲ ወደብ በኩል ለ325,817 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ የኢንስፔክሽን አገልግሎቶች መስጠት የቻለ ሲሆን የተቋሙ የሩብ ዓመት የስራ እንቅስቃሴ አሁን በደረሰበት ደረጃ ሲታይ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን የማስፋት ስራዎችን ጨምሮ የሩብ ዓመቱ አፈፃፀሙ ዓመታዊ እቅዱን በታቀደው መሰረት እንደሚፈፅም አመላካች መሆኑን የድርጅቱ የሥራ አመራር አባላት የሩብ ዓመት አፈፃፀሙን በገመገሙበት ወቅት ገልፀዋል፡፡

    አዳዲስ የተስማሚነት ምዘና እና ተዛማጅ ተግባራትን በመጀመር የተግባር ወይም ሙያዊ ስልጠና በመስጠት አቅምን ለመገንባት በታቀደው መሰረት ኢተምድ ከBureau Veritas (BV) ጋር ባደረገው ለአንድ አመት የሚቆይ ስምምነት የእውቅና ወሰን ማስፋት፣የባለሙያዎች ስልጠና እና የአቅም ግንባታ የድጋፍና የማማከር አገልግሎት በፍተሻ ላብራቶር፣ በኢንስፔክሽንና በሰርቲፊኬሽን የደረጃ መስፈርቶችና የስራ መመሪያዎች ላይ ለዋና የስራ ሂደቶችና ለደጋፊ የስራ ሂደት ሰራተኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይም የሶማሌላንድ የጥራት ቁጥጥር ኮሚሽን ከኢትዮጵያ የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ መሰረት የተጀመሩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በኢተምድ ባለሙያዎች  በሁለት ዙር ተሰጥቷል፡፡

ኢተምድ የሚሠጠውን አገልግሎት በእቅድ መሰረት ለማከናወን ተቋማዊ አደረጃጀትን በሠው ኃይል እና በግብዓት በማደራጀት፤የተቋሙን አገልግሎቶች በማስተዋወቅና በመሸጥ፣ በሁሉም የአገልግሎት ዘርፎች ያሉትን ዓለም አቀፍ ዕውቅና የማስጠበቅ እና አዳዲስ የማግኘት ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ እየተሰራ ቢሆንም ከዚህ በበለጠ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ  ተጠቅሷል፡፡ ኢተምድ ደረጃቸውን የጠበቁና ደህንነታቸው የተረጋገጠ ምርቶች ወደ ገበያ እንዲቀርቡና ተስማሚ ባልሆኑ ምርቶች ከሚደርስ ኪሳራ ህብረተሰቡን፣አካባቢን እና የሀገርን ኢኮኖሚ ለመጠበቅ የሚያስችል አገልግሎት በመስጠት የበኩሉን አስተዋፅኦ እየተወጣ ይገኛል፡፡