ኢተምድ በ120 የፍተሻ ወሰኖች እውቅና አገኘ፡፡

ኢተምድ በ120 የፍተሻ ወሰኖች እውቅና አገኘ፡፡

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት በአንድ መቶ ሃያ የተለያዩ የፍተሻ ወሰኖች የእውቅና ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት አገኘ፡፡ ድርጅቱ ግንቦት 09 ቀን 2014ዓ.ም በአዲስ አበባ ኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል በተከናወነው የእውቅና ማረጋገጫ ሰርቲፍኬት አሰጣጥ ስነስርዓት ላይ እውቅናውን ያገኘው ከኢትዮጵያ የአክሪዲቴሽን አገልግሎት ሲሆን የእውቅና ሰርተፊኬቱን አቶ ተሻለ በልሁ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር እና አቶ አቤል አንበርብር የድርጅቱ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተቀብለዋል፡፡

ኢተምድ እውቅና ያገኘባቸው 120 ወሰኖች፤ 48 ነባር እና 72 አዳዲስ ወሰኖች በምግብና መጠጥ የፍተሻ ላቦራቶር ፣ በኬሚካልና የማዕድን የፍተሻ ላቦራቶር፣ በግብርና እና የግብርና ግብዓት የፍተሻ ላቦራቶር፣ በማይክሮ ባዮሎጂ የፍተሻ ላቦራቶር፣ በኤሌክትሪካል የፍተሻ ላቦራቶር፣ በሜካኒካል ፍተሻ ላቦራቶር፣ በጨርቃ ጨርቅና የስቴሽነሪ የፍተሻ ላቦራቶር እና በቆዳና የማሸጊያ ምርቶች የፍተሻ ላቦራቶር ላይ የተለያዩ ፍተሻዎችን ለማከናወን ያስችላሉ፡፡

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በልሁ በሰርቲፊኬት አሰጣጥ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ድርጅቱ በ120 ወሰኖች እውቅና ማግኘቱ በኢንዱስትሪም ሆነ በግብርና የተመረቱ ምርቶች ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ገበያ በሚቀርቡበት ጊዜ በኢተምድ አገልግሎቶች ስርዓት ውስጥ ማለፋቸው የምርቶቹን ተቀባይነት በማሳደግ ነፃ የሆነ የሸቀጦች ምልልስ በመፍጠር ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈተሸ ምርት ያለምንም ዳግም ፍተሻ ወደሌላ ሀገር እንዲገባ ለማስቻል ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡