የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት ያስገነቡትን የስፖርት ማእከል መረቁ

የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት ያስገነቡትን የስፖርት ማእከል መረቁ

ግንቦት 26 ቀን 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት (ኢተምድ) የኢፌዲሪ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር የጥራት መሰረተ ልማት ማረጋገጫ ዘርፍ ሚ/ዲኤታ ክቡር አቶ እንዳለው መኮንን በተገኙበት ከሶስቱ የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ለሰራተኞች የስፖርታዊ እንቅስቃሴ አገልግሎት መስጫ ማእከል አስመረቁ፡፡ በምርቃት  ፕሮግራሙ ላይ የአራቱም የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት የስራ አመራር አባላት በጋራ የኤሮቢክስ የስፖርት እንቅስቃሴ ሰርተዋል፡፡

ክቡር እንዳለው መኮንን በምርቃት ስነ-ስርዓቱ እንደተናገሩት ከእንቅስቃሴ አልባ  የኑሮ ዘይቤና የስራ ባህሪ አንፃር ሰራተኞች ለረጅም ሰዓት ተቀምጠው አልያም ቆመው የእለት ተእለት ስራቸውን መስራታቸው በጤንነታቸው ላይ ተፅእኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት ለሰራተኞቻቸው ጤንነትና ደህንነት እንዲሁም ለሌሎች መስሪያ ቤቶች አርአያ ለመሆን የሚያስችላቸውን ሰራተኞች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ጂምናዝም፣ የስቲምና የሳውና ባዝ አገልግሎት መስጫ ማእከል ወደ ተግባር መግባቱ ውጤታማ የሥራ አፈፃፀም ለማስመዝገብ እንደሚያስችል በመግለፅ ለወደፊቱም ውጤታማ የስራና የጤንነት መጠበቂያ ጊዜ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ ብለዋል፡፡

በየቀኑ መጠነኛና ጤናማ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ማድረግ የሰውነት የክብደት መጠንን ለመቀነስ ፣ ደስተኛ ለመሆን፣ ለጡንቻ እና ለአጥንት ጥንካሬ ፣ የሰውነት አቅምን ለማሳደግ ፣ በበሽታ የመጠቃት እድልን ለመቀነስ፣ የተስተካከለ የደም ዝውውር  እንዲኖር ፣ ለአዕምሮ ጤና እና ለማስታወስ ችሎታ፣ ዘና ላለ ስሜት እና ለተስተካከለ እንቅልፍ፣ ሥር የሰደደ ሕመም እንዳይሰማ ለማድረግ፣ አዎንታዊ አስተሳሰብ እንዲዳብር፣ በራስ የመተማመን ስሜት ለማሳደግ እንዲሁም ስራን በብቃት፣ በቅልጥፍና እና በውጤታማነት ለማከናወን ያስችላል፡፡